"በ16 ዓመቴ ያለፈቃዴ የአእምሮ ምርምር ያደረገብኝ ሲአይኤን እከስሳለሁ"

ላንግ ፖሊንግ በልጅነቷ

የፎቶው ባለመብት, Submitted photo

የምስሉ መግለጫ, ላንግ ፖሊንግ በልጅነቷ

ላንግ ፖሊንግ ወደኋላ መለስ ብላ አለን ሜሞሪያል የሥነ ልቦና ሕክምና ተቋምን ስታስታውስ ከአእምሮዋ የማይጠፋው የመድኃኒት ጠረን ነው።

"ሆስፒታል አይመስለኝም ነበር። በጣም እንደጠላሁት አስታውሳለሁ" ትላለች።

እአአ በ1958 በሆስፒታሉ ለአንድ ወር ቆይታለች። ያኔ 16 ዓመቷ ነበር።

"ታዛዥ እንዳትሆን ያደረገ የአእምሮ መዛበት" ገጥሟታል በሚል አንድ ዳኛ ሆስፒታል እንድትገባ ወስነው ነበር።

በዚህ ሆስፒታል ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ምርምር ያደርግ ነበር።

የሰዎችን አእምሮ ለመቆጣጠር የተደረገው የሲአይኤ ምርምር በከፍተኛ ምሥጢር የተያዘ ነበር።

ላንግ እና አንድ ሌላ ተጎጂ በምርምሩ ጉዳት ከደረሰባቸው ካናዳውያን ጋር በመሆን ክስ መሥርተዋል። ሆስፒታሉ አቤቱታ ቢያሰማም የክስ ሒደቱ እንዲቀጥል ፍርድ ቤት ወስኗል።

ላንግ የሕክምና ሰነዷን ያገኘችው በቅርቡ ነው።

ወላጆቿ ከኦታዋ ወደ ሞንትሪያን ሲዛወሩ ለውጡን መቋቋም አልቻለችም ነበር። ከቤተሰቦቿ ፈቃድ ውጭ ከጓደኞቿ ጋር ለመገናኘት ከቤት ኮብላለች በሚል የሕክምና ሰነዷ ላይ ሰፍሯል።

"እንደማንኛውም ወጣት ነበርኩ። ዳኛው ግን ሆስፒታል እንድገባ ፈረደ" ስትል ታስታውሳለች።

ሲአይኤ 'MK-Ultra' በሚል ስያሜ ያካሂድ የነበረው ምሥጢራዊ ምርምር ውስጥ ተሳታፊ ሆነች።

አእምሮ ላይ ለውጥ የሚያመጡ እንደ ኤልኤስዲ ያሉ መድኃኒቶች እና አእምሮን በኤሌክትሪክ ሾክ ማከም ላይ ምርምር ይካሄድ ነበር።

ሰዎች ፈቃድ ሳይሰጡ አስተሳሰባቸውን መቀየር (brainwashing) የጥናቱ አንደኛው ግብ ነበር።

በአሜሪካ እና በካናዳ ከ100 በላይ በሚሆኑ ሆስፒታሎች፣ ማረሚያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶት ውስጥ ምርምሩ ተካሂዷል።

በአለን ሜሞሪያል የሥነ ልቦና ሕክምና ተቋም ውስጥ ዶ/ር ኤርዊን ካሜሩን የተባሉ ባለሙያ ለታካሚዎች መድኃኒት በመስጠት ንግግራቸውን ይቀርጹ ነበር። ድርጊቱን ወደ አንድ ሺህ ጊዜ ደጋግመው ፈጽመዋል።

ላንግ አንድ የድምጽ ቅጂን መቶ ጊዜ ደጋግማ እንድትሰማ ተደርጋለች።

"አንቺ ጥሩ ልጅ ነሽ፤ አንቺ መጥፎ ልጅ ነሽ የሚለውን የድምጽ ቅጂ ከመቶ ጊዜ በላይ ሰምቼዋለሁ" ትላለች።

የሥነ ልቦና ተመራማሪ ጆርዳን ቶርቢ እንደምትለው፤ ቃላትን በመደጋገም ታካሚዎች አእምሮ ላይ ለውጥ የማምጣት ስልት ሲሆን ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተከተለ አሠራር አይደለም።

አለን ሜሞሪያል የሥነ ልቦና ሕክምና ተቋም
የምስሉ መግለጫ, አለን ሜሞሪያል የሥነ ልቦና ሕክምና ተቋም
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእንቅልፍ መድኃኒት በመስጠት፣ ዕይታን ሆነ ብሎ በመጋረድ እና ኮማ ውስጥ በማስገባትም ሕክምናው ይከናወናል።

ላንግ እንደምታስታውሰው ኤልኤስዲ፣ ሶድየም አምያታል፣ ባርቢቱሬት እንዲሁም ራስን የሚያስተው ኒትሮስ ጋዝ እና ሌሎችም መድኃኒቶች ተሰጥተዋታል።

በወቅቱ ምርምሩ ሲደረግባት "ኒትሮስ ኦክሳይድ ሲሰጣት በጣም ቁጡ እና ኃይለኛ ሆናለች። እራሷን ከአልጋ እየወረወረች ስትጮህ ነበር" በማለት ሐኪሙ ስለ ላንግ ጽፈዋል።

የሲአይኤ ምሥጢራዊ ምርምር ያደረሰው ጉዳት ይፋ መውጣት የጀመረው እአአ በ1970ዎቹ ነው።

በአሜሪካ እና በካናዳ የሚኖሩ ተጎጂዎች ለመክሰስ ሞክረዋል። አሜሪካ የተከፈቱ ክሶች ስኬታማ አልሆኑም። በ1988 የካናዳ ዳኛ የአሜሪካ መንግሥት ለእያንዳንዱ ተጎጂዎች 67,000 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ወስነዋል።

በ1992 የካናዳ መንግሥት ለ77 ተጎጂዎች ለእያንዳንዳቸው 80,000 ዶላር ካሳ ሰጥቷል።

ላንግ ካሳ ከተሰጣቸው መካከል አይደለችም። ምርምር ሲካሄድባት እንደነበረ ያወቀችው በቅርቡ ነው። ለዓመታት አንዳች ችግር እንዳለባት ሲሰማት ቆይታለች።

በሆስፒታሉ ከደረሰባት ጥቂቱን ብቻ ነው የምታስታውሰው። አሁን የአራት ልጆች አያት ሆናለች። ከሆስፒታሉ ወጥታ ሁለት ልጆች ብታፈራም ለዓመታት ጠባሳው አልለቀቃትም።

"ሙሉ ዕድሜዬን የማስብበት መንገድ የተለየ መሆኑ ያስጨንቀኝ ነበር። ለምን እንዲህ አስባለሁ? ብዬ እገረማለሁ። እዚያ [ሆስፒታል] ሳለሁ የደረሰብኝ ነው ለዚህ ሁሉ ያበቃኝ" ትላለች።

ሙሉ ሕይወቷን ያሳለፈችው ከአእምሮ ጤና እክል ጋር በመታገል ነው። ብዙ መድኃኒቶችንም ትወስዳለች። አስፈሪ ሕልሞች በማየት እንደምትሰቃይም ትናገራለች።

"አንዳንድ ሌሊት እየጮህኩ ከእንቅልፌ እነቃለሁ" ስትል ትገልጻለች።

ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ስለሆነ ሆስፒታሉ ለቢቢሲ አስተያየት ለመስጠት አልፈቀደም።

ላንግ ከደረሰባት ስቃይ ነጻ ለመውጣት የፍርድ ቤት ውሳኔን እየተጠባበቀች ነው።

"አንዳንዴ ቤት ቁጭ ብዬ ያሳለፍኩትን አስባለሁ። የዶ/ር ኤርዊን ካሜሩንን ምሥል ካየሁ በጣም ነው የምበሳጨው።"

ዶ/ር ኤርዊን ካሜሩን ስማቸው ከሲአይኤው ምሥጢራዊ ምርምር ጋር ተያይዞ ቢነሳም፤ በወቅቱ ጥናቱን ሲያካሂዱ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ የነበው ሲአይኤ መሆኑን መረጃው እንደሌላቸው የሥነ ልቦና ተመራማሪዋ ጆርዳን ቶርቢ ትናገራለች።

በ1964 ከሲአይኤ ጋር የነበራቸው ሥራ እንደተቋረጠ ብዙም ሳይቆዩ በልብ ድካም ሞተዋል።

የሥነ ልቦና ተመራማሪዋ ጆርዳን ቶርቢ እንደምትለው፤ ባለሙያው ለጥናታቸው ገንዘብ የሚመድበው የትኛው ተቋም እንደሆነ ቢያውቁም ባያውቁም ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ምርምር ማድረግ አልነበረባቸውም።

"ታካሚዎቹ ያጡትን መልሰው አያገኙም። ግን ስቃያቸው ችላ ተብሎ እንዳልታለፈ ሊያውቁ ይገባል። ሌሎችም ከዚህ እንዲማሩ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሚና ይኖረዋል" ስትልም ታክላለች።