ግብፅ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞችን ማሰሯ እና ማባረሯ ተነገረ

የግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ

የፎቶው ባለመብት, Anton Aleksenko

የምስሉ መግለጫ, የግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ

ግብፅ በቅርቡ ከ150 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞችን "በይፋ ባልተገለጸ ምክንያት" ሁኔታ ከአገር ማባረሯን በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ኤርትራውያን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናገሩ።

ይህ እርምጃ የተወሰደው ኤርትራውያኑ በብዛት ከሚኖሩበት የካይሮ ከተማ አካባቢ እንዲወጡ ተደርጎ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ለወራት ከታሰሩ በኋላ መሆኑን በግብፅ የሚኖረው ኤርትራዊ አድል (ስሙ የተቀየረ) ተናግሯል።

ሌሎች ኤርትራውያን በበኩላቸው ይህ ስደተኞቹን የማስወጣት እርምጃ አሳሳቢ የሆነው ዒላማ ያደርገው ሴቶች እና ፈቃድ ያላቸውን ጭምር ያካተተ መሆኑ ነው።

አንዳንዶች ከሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ ተይዘው መወሰዳቸውን አድል ጨምሮ ተናግሯል።

አድል አክሎም አንዲት ሴት ከሥራ ቦታዋ ተይዛ ልጇን ትታ መታሰሯን ገልጾ ልጇ ጓደኞቿ ጋር ለተወሰነ ቀን ከቆየ በኋላ ከግብፅ ልትባረር ትችላለች በሚል ስጋት ጓደኞቿ ልጁን እስር ቤት ድረስ ይዘውላት ቢሄዱም የግብጽ ፖሊሶች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እናትና ልጅ ተለያይተው እንደሚገኙ ተናግሯል።

ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው ስደተኞች እንደሚሉት አብዛኞቹ ኤርትራውያኑ ከአንድ አስከ ሦስት ወራት በእስር ቤት ከቆዩ በኋላ ወደ አገራቸው የሚባረሩት በኤርትራ ኤምባሲ በኩል ነው።

ኤርትራውያን ስደተኞች በተለይም ለረዥም ጊዜ በግብፅ ውስጥ የኖሩት ከባድ ችግር እንደገጠማቸው ገልፀው፣ እስሩ እና ከአገር ማባረሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተባባሰ መምጣቱን ይናገራሉ።

ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረው እና ግብፅ ውስጥ ለረዥም ዓመታት የኖረው ሸምድሃን የተባለ ኤርትራዊ እንደሚለው በተለይ ሱዳን ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በርካታ ስደተኞች ወደ ግብፅ መግባታቸው ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ከዚህ ቀደምም ከስደተኞች ፈቃድ ወረቀት ጋር በተያያዘ እስር እና ከአገር ማባረር የነበረ ቢሆንም፤ የአሁኑ ግን በአገሪቱ ካለው የኢኮኖሚ እና የምንዛሪ ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው።"

ሸምድሃን እንደሚያስረዳው የግብፅ ፓወንድ ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሪ ዋጋ ባለፉት ሦስት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት በሚል ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ገንዘብ መንዛሪዎችን እያደነ መሆኑን ተናግሯል።

የግብፅ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ክፉኛ በማሽቆልቆሉ የመሠረታዊ ፍጆታዎች እና የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ኤርትራውያኑ ይናገራሉ።

በዚህም የተነሳ የአገሪቱ ዜጎች ከማማረር አልፈው ለችግሩ አንዱ ምክንያት በአገራቸው የበዙት የውጭ አገር ስደተኞች መሆናቸውን በመግለጽ እንደሚያምርሩ እና አንዳንዴም እንደሚተናኮሉ ኤርትራውያን ይጠቅሳሉ።

በተጨማሪም ግብፃውያን በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚያሰሙት ቅሬታ ከአገሬው በተለየ የሚከተሉት የአለባበስ ዘይቤ፣ አልኮል መጠጥ እና ጸብ መሆኑን ካይሮ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን ቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

በአንድ ወቅት በኤርትራውያን እና በግብፃውያን መካከል የቡድን ጸብ አጋጥሞ የነበረ ሲሆን በጉዳዩ ውስጥም በካይሮ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ገብቶ ከአገሪቱ የፀጥታ ኃይል ጋር በመሆን ስምምነት መፈጠሩን ስደተኞች ያስታውሳሉ።

በአሁኑ ወቅት ኤርትራውያን ስደተኞችን ከግብፅ በግዳጅ ወደ አገራቸው የመመለሱ እርምጃ በበርካታ ኤርትራውያን ዘንድ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም ካይሮ በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ እውቅና እንደሚካሄድ አድል ተናግሯል።

ባለፉት ወራት ቢያንስ 150 ያህል ኤርትራውያን ከግብፅ ወደ አገራቸው የተባረሩ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የስደተኛ ማኅበረሰቦች ሁሉ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑን ኤርትራውያኑ ገልጸዋል።

ኤርትራውያኑን የማባረሩ ሂደት የሚከናወነው ወደ ኤርትራ ኤምባሲ ከተወሰዱ በኋላ ሲሆን፣ ወደ አገራቸው መመለስን እንዲቀበሉ እንደሚገደዱ እና መመለስ የማይፈልጉት ደግሞ ያለምንም ፍርድ በእስር ላይ እንዲቆዩ ይደረጋሉ በማለት ኤርትራውያኑ ሂደቱን ያስረዳሉ።

ነገር ግን ኤምባሲው ሕጋዊ የስደተኝነት ምዝገባ ወረቀት ያላቸውን ኤርትራውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደማያስገድድ ኤርትራውያን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ትግርኛ በግብፅ የሚገኘውን የኤርትራ ኤምባሲን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

ከግብፅ የተባረሩት ኤርትራውያን አገራቸው ሲደርሱ ምንም ችግር ሳያጋጥማቸው ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱ የተነገረ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ግን ዳግም በሱዳን ወይም በኢትዮጵያ በኩል ተመልሰው ወደ ስደት እንደሚያቀኑ ኤርትራውያኑ ገልጸዋል።

ግብፅ ስደተኞችን ከግዛቷ የማስወጣት እርምጃ አዲስ ነገር ባይሆንም፣ ከዚህ በፊት ግን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) አማካኝነት ጠበቃ ቆሞላቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መፍትሄ ያገኝ እንደነበር የሚጠቅሱት ስደተኞቹ "አሁን ግን የሚሰማን የለም" ሲሉ ያማርራሉ።

በእስር ቤት ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩት ስደተኞቹ ለመጠየቅ እና አንዳንድ ድጋፎችን ለማግኘት ለፖሊሶች እና ለባለሥልጣናት ጉቦ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብፅ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የሁለቱ አገራት መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ አንዳቸው በሌላቸው አገር ውስጥ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።