ከባድ ራስ ምታትን የሚቀሰቅስብን ምንድን ነው? መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

ጭንቅላቷን የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ራስ ምታት ሁላችንም ከሞላ ጎደል በአንድ ወቅት የሚገጥመን ነገር ነው።

ራስ ምታታችን ከሁለት ደቂቃዎች እስከ ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ።

ሕመሙም ጠንካራ፣ ቶሎ የማይለቅ፣ ዓይን መግለጥ እስከመቸገር ሊደርስ የሚችል ወይም ውጋት ያለው እና አንዳንድ ጊዜ ከራስ ቅል አልፎ ወደ ቆዳ፣ ፊት፣ አንገት ድረስ የሚሠራጭ ሊሆን ይችላል።

የቢቢሲን የጤና ፖድካስት የሚያቀርበው ዶ/ር ዣንድ ቫን ቱሌከን ይህንን የሕመም ስሜት በደንብ የሚያውቀው መሆኑን ይናገራል።

በወር አንድ ጊዜ ወይም በየስድስት ሳምንቱ ራስ ምታት ያጋጥመዋል።

እናም ሕመሙን ሲገልጸው "የሆነ ሰው የዓይኔን ኳስ ከውስጥ እየቦረቦረ እንዳለ ዓይነት ስሜት ይሰማኛል" በማለት ነው።

በብሔራዊ ማይግሪን ማዕከል ውስጥ ዶክተር የሆኑት ኬቲ ሙንሮ ከመጥፎ ራስ ምታት ጀርባ ምን ሊኖር ይችላል ብሎ መደናገጥ ያለ ቢሆንም እምብዛም ከባድ ነገር አይደለም ይላሉ።

"የሆነ ነገር ተፈጥሯል ብሎ መጨነቅ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ግን እንደዚያ የመሆን ዕድሉ በጣም ትንሽ ነው" ሲሉ ይገልፁታል።

"እንዲህ ዓይነት የከፋ ራስ ምታት የመጀመሪያዎ ከሆነ ዶክተር ቢያይዎት መልካም ነው" ሲሉ ይመክራሉ።

ነገር ግን ቀለል ያለ እና ተደጋጋሚ ራስ ምታት እያጋጠመዎት ከሆነ የሕክምና ባለሙያ ጋር ከመሄድ ባሻገር በቤት ውስጥ ሊሞክሯቸው የሚችሏቸው ጥቂት ቀላል ነገሮች አሉ።

ምን ያህል እክል ፈጥሮብዎታል

ዶ/ር ዣንድ የራስን ራስ ምታት መረዳት በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠቃሚ መሆኑን ይገልጻል።

ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ አንድ ወጥ ምክንያት ስለሌላቸው ማስታወሻ መያዝ ድግግሞሹን ለመረዳት እና የሚቀሰቅስብዎትን ምክንያት ለማወቅ ይረዳዎታል።

ለአንዳንድ ሰዎች እንደ ነጎድጓድ እና መብረቅ ያሉ የአየር ሁኔታዎች፣ ለሌሎች ደግሞ ለብርሃን መጋለጥ የሚቀሰቅሱባቸው ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

ዶ/ር ሙንሮ "ለእኔ በጣም መጥፎው ጊዜ በቅዝቃዜ ወቅት መኪና ስነዳ እና ፀሐይ እየጠለቀች ስትሄድ፣ በዛፎች መካከል የምትፈጥረው ብልጭታ...በጣም ያባብስብኛል" ብለዋል።

የሚከተሉት ግን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡-

  • ራስ ምታቱ ሲጀምር ምን እያደረጉ ነበር?
  • ምን ነበር የተመገቡት? የጠጡትስ?
  • ምን ያህል ጥሩ እንቅልፍ አግኝተዋል?
  • የአየሩ ሁኔታ
  • ለሴቶች ደግሞ ራስ ምታት ከሆርሞን ለውጥ ጋር ሊገናኝ ስለሚችል የወር አበባ ዑደትን መከታተል ተገቢ ነው።

ዶ/ር ሙንሮ ይህንን ከመጠን በላይ ማብዛትም አስፈላጊ አለመሆኑን ይመክራሉ።

"ስለራሴ ራስ ምታት በጣም ዝርዝር ውስጥ በመግባቴ ተሳስቻለሁ፤ ይህም ተስፋ አስቆራጭ ነበር። ይልቁንስ ቀላል አድርገው ምናልባት በቀንዎ ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ ለማጠቃለል ከአንድ እስከ 10 ቁጥር በመጻፍ ይግለፁት።

"ይሀም መጥፎዎቹን ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ጥሩ ቀናት እንዳሳለፉ ለመከታተል ጠቃሚ ነው። ከዚያም ዶክተርዎ ያንን በማየት የሕመምዎን ደረጃ ለመለየት ሊረዳዎት ይችላል።"

ጭንቅላቷን ያያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካፌይን በተገቢው መንገድ ይጠቀሙ

ራስ ምታት ካለብዎ ካፌይን (ቡና እና ሻይን የመሳሰሉ ነገሮች ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር) ማስወገድ እንዳለብዎት ያስቡ ይሆናል ነገር ግን ዶ/ር ሙንሮ እውነታ ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ነው ይላሉ።

ጥንቃቄ በተሞላበት እና አነስተኛ መጠን የሚወሰድ ከሆነ የሕመም ማስታገሻዎችን የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል። ነገር ግን በየቀኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ካፌይን መውሰድ አይኖርብዎትም።

"ካፌይን የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት እንዲሠራ ሊያግዝ ይችላል" ሲሉ ዶ/ር ሙንሮ ያስረዳሉ። ነገር ግን እንቅልፍዎ እንዳይረበሽ ከሰዓት በኋላ እና ማታ ላይ ከመውሰድ ይቆጠቡ።

በሰፊው ግን ምን ያህል የካፌይን መጠን እንደሚወስዱ መከታተል ተገቢ ነው።

በየቀኑ ብዙ ካፌይን መውሰድ ራስ ምታት የሚያስከትል ሲሆን በድንገት ካቆሙም እንዲሁ የለመዱትን ካፌይን በማጣት ራስ ምታት ሊያጋጥምዎ ይችላል።

ምግብዎን አይዝለሉ

በራስ ምታት የሚሰቃዩ ከሆነ የሚመገቧቸው ነገሮች እና የሚመገቡበት ጊዜ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ማስተዋል ተገቢ ነው።

ዶ/ር ሙንሮ በፕሮቲን፣ በጤናማ ስብ እና በካርቦሃይድሬት የበለፀገ አመጋገብን መከተል የኃይልዎን ደረጃ ለማረጋጋት ይረዳል ሲሉ ይመክራሉ።

ጣፋጭነት ያላቸው የታሸጉ ምግቦችን እንዲሁም ምግብዎን በሰዓቱ አለመመገብን ያስወግዱ።

ዶክተር ሙንሮ የራስ ምታትዋ የወተት ተዋጽኦ እና ግሉተን ያላቸው ምግቦችን መመገብ ስታቆም እንደተዋት ትናገራለች። በእርግጥ እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች ለሁሉም የሚሠሩ አይደሉም።

"በተጨማሪም አዘውትሬ መመገብ እና ወደ ሥራዬ ቦታ ምሳዬን ይዤ በመሄድ መመገብ መጀመሬ ለውጥ አምጥቻለሁ" ትላለች።

ዶ/ር ሙንሮ ስለ ምግብ ከማሰብ በተጨማሪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጥሩ እንቅልፍ ማጣት፣ ጭንቀትን መቆጣጠር እና ውሃ መጠጣት የራስ ምታትን ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል።

በቀን ውስጥ በቂ ውሃ መጠጣት ሽንትዎ ጥርት ያለ ቀለም እንዲኖረው እና መጠማት አንዳይሰማዎት ያደርጋል።

4. ኮዴይን ያለባቸው የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን አይውሰዱ

ዶክተር ሙንሮ "እንደ ሕመም ማስታገሻዎች ወይም ማቅለሽለሽ ለማስቀረት የሚረዱ ኪኒኖች ራስ ምታትን ለመቆጣጠር ያለ ሐኪም ማዘዣ መግዛት የሚቻሉ ብዙ መድኃኒቶች አሉ" ብለዋል ።

አንዳንድ ራስ ምታት በተደጋጋሚ እንዲከሰት እና እንደ ማቅለሽለሽ ያሉ ምልክቶችን ሊያባብስ ስለሚችል "ኮዴይንን ከያዘ ማንኛውም መድኃኒት" ከመውሰድ መቆጠብ አለብዎት ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

"የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች በጥሩ ሁኔታ ሊሠሩ የሚችሉ ቢሆንም ይህ ግን የራስ ምታትዎ ምን ያህል ከባድ በመሆኑ ላይ ይወሰናል።"

"በጣም እየደጋገሙ ወይም እየጠነከሩ ከሄዱ፣ ሐኪምዎ ይበልጥ ተስማሚ የሆነ መድኃኒት እንዲያገኙ ሊረዳዎት ይችላል።"

የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ውጤታማነታቸው ላይ የራሱ ተጽዕኖ ስላለው በሳምንት ከሁለት ቀን በላይ አለመውሰድዎን እርግጠኛ ይሁኑ።