ትራምፕ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚከፈልበትን 'ጎልደን ካርድ' ቪዛ ይፋ አደረጉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, @realDonaldTrump/Truth Social

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢያንስ 1 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ለሚችሉ ቱጃር የውጭ አገር ዜጎች የሚሰጥ ጎልደን ካርድ ቪዛ አስጀመሩ።

ይህንን ቪዛ ለማግኘት የሚያመለክቱ ግለሰቦች ብቁ መሆናቸው በሚገባ ታይቶ ከተረጋገጠ "ቀጥታ ዜግነት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ይከፈትላቸዋል" ተብሏል።

ትራምፕም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "እጅግ የሚያስደንቅ ነገር! ታላላቅ የአሜሪካ ኩባንያዎቻችን በስተመጨረሻም አቻ የማይገኝለት ተሰጧቸውን ጠብቀው ማቆየት ይችላሉ" ሲሉ ጽፈዋል።

የትራምፕ ጎልድ ካርድ ፕሬዚዳንቱ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ይጀመራል ተብሎ ነበር።

ይህንን ካርድ የሚያስተዋውቀው ድረ ገጽ ላይ በሰፈረው መረጃ መሠረት ጎልድ ካርድ ቪዛ ሲሆን ቪዛውን የሚያገኙ ለአገሪቱ "ተጨባጭ ጥቅም ያስገኛሉ" ይላል።

ይህ የቪዛ ዓይነት ይፋ የሆነው የትራምፕ አስተዳደር ሕገወጥ ስደተኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደሩ የስራ ቪዛ ለማግኘት የሚከፈለውን ገንዘብ ከፍ ሲያደርግ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደ አገራቸው እየመለሰ ነው።

ጎልድ ካርድ የተባለው ይህ የቪዛ ፕሮግራም ድረገጽ ላይ "አሜሪካን በተጨባጭ እንደሚጠቅሙ ማስረጃ ማቅረብ ለሚችሉ" አመልካቾች "በአጭር ጊዜ ውስጥ" የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠት ቃል የሚገባ ሲሆን 1 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ይጠይቃል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህንን ቪዛ ለማግኘት ለሠራተኞቻቸው የሚያመለክቱ ድርጅቶች 2 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ የሚጠበቅ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ክፍያዎችም ይኖርባቸዋል።

ይህ የቪዛ ዓይነት "ፕላቲኒየም" ደረጃ አለው የተባለ ሲሆን፣ 5 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ለሚችሉ ደግሞ ልዩ የታክስ እፎይታ ጊዜ እንደሚሰጥ በድረ ገጹ ላይ ተመልክቷል።

እንደ አመልካቹ ሁኔታ ተጨማሪ ክፍያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በድረገፁ ላይ ተገልጿል።

ግለሰቦች ማመልከቻቸው ከመታየቱ በፊት ሂደቱን ለማስጀመር የሚያስችል 15ሺህ ዶላር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ጎልድ ካርድ የተባለው ይህ የቪዛ ዓይነት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጀመርያ ላይ ይፋ ሲሆን በርካታ ትችቶች ቀርበውበት ነበር።

አንዳንድ ዲሞክራቶች ጥቂት ቱጃሮችን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሚጠቅም ሲሉ ነቅፈውታል።

ትራምፕ ይህንን ዕቅዳቸውን ሲናገሩ ቪዛውን ከግሪን ካርድ ጋር ተመሳሳይ ነው ብለው ነበር።

ይህም የተለያየ የገቢ ደረጃ ያላቸው ስደተኞች በአሜሪካ በቋሚ ለመኖር እና ለመሥራት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል የሚል ነበር።

የአሜሪካ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦች ከአምስት ዓመት በኋላ ዜግነት ለመጠየቅ ብቁ ይሆናሉ።

ትራምፕ ጎልድ ካርድ በተለየ "ከፍተኛ ብቃት "ያላቸው ባለሙያዎችን ዒላማ ያደረገ ነው ካሉ በኋላ "አምራች የሆኑ ሰዎችን እንፈልጋለን" ብለዋል።

"5 ሚሊዮን ዶላር መክፈል የሚችሉ ሰዎች ስራ መፍጠር ይችላሉ" ያሉት ትራምፕ "እንደ ጉድ ሊቸበቸብ ይችላል። ሽሚያ ነው የሚሆነው" ብለዋል።

ይህ የቪዛ ፕሮግራም ይፋ የሆነው የትራምፕ አስተዳደር ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ከፍተኛ ገንዘብ እና የሰው ኃይል መድቦ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ትራምፕ የጉዞ እገዳ ከጣሉባቸው 19 አገራት የመጡ ስደተኞች ማመልከቻዎች እንዲቆም አድርገዋል።

አስተዳደሩ በተጨማሪም በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን የተሰጡ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዶችን ዳግም እፈትሻለሁ በሚል የትኛውም የጥገኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ እንዲቆም አድርጓል።

በመስከረም ወር ለውጭ አገር ዜጎች የሚሰጠው የሥራ ቪዛ አመልካቾች 100 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ የሚያደርግ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

ይህ ውሳኔ የውጭ አገር ተማሪዎችን እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ያስደነገጠ ነበር።

ዋይት ሐውስ በኋላ ላይ ክፍያው አዲስ አመልካቾች ላይ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጿል።