በሶማሊያውያን ላይ ፊታቸውን ያዞሩት ትራምፕ እና ባለፉት ዓመታት አሜሪካ በሶማሊያ ውስጥ የነበራት ሚና

የአሜሪካ ወታደሮች በሶማሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶናልድ ትራምፕ የአፍሪካ ቀንድ አገሯን ሶማሊያን "አስቀያሚ"፣ ሶማሊያውያንን ደግሞ ከአሜሪካ መወግድ ያለባቸው "ቆሻሻ" በማለት አንቋሽሸዋል።

ሶማሊያውያንን "ዝም ብለው መገዳደል ነው ሥራቸው" ሲሉም በዋይት ሐውስ ከባለሥልጣኖቻቸው ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

አክለውም በርካታ የሶማሊያ ማኅበረሰብ በሚኖሩባት የሜኒሶታ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ስደተኞች ላይ እርምጃ እንዲወሰድም አዘዋል።

በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ትውልደ ሶማሊያዊት የምር ቤት (ኮንግረስ) አባል ኤልሃን ኦማር የተመረጠችው ከዚሁ ከሜኒሶታ ግዛት ነው።

ኤልሃን ኦማር እና ዶናልድ ትራምፕ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ቃላት ተለዋውጠዋል።

ሜኒሶታ "ሕገ ወጥ ገንዘብ ወደ ሕጋዊ መስመር የሚገባበት" ግዛት ነውም ብለዋል ትራምፕ።

ለበርካታ ሶማሊያውያን ከለላ የሚሰጠው የስደተኞች ጥበቃ ሕግ እንዲሰረዝም ጫና እያሳደሩ ነው።

በኮቪድ-19 ወቅት ለልጆች ምግብ ለማቅረብ በሚል የሜኒሶታን መንግሥት አጭበርብረዋል የተባሉ ሰዎችን የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ከስሷል።

በማጭበርበሩ ስማቸው የተነሳው ሰዎች ከአጠቃላዩ የሜኒሶታ ሶማሊያዊውያን ነዋሪዎች አንጻር ውስን ቁጥር ነው ያላቸው። ሆኖም ግን ትራምፕ ማኅበረሰቡን በጅምላ ፈርጀዋል።

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በማጭበርበሩ የተሳተፉት 59 ሰዎች ሲሆኑ የተመዘበረው ገንዘብ ደግሞ አንድ ቢሊዮን ዶላር ነው።

በተፈጸሙት ሦስት የማጭበርበር ወንጀሎች ላይ አሁንም ምርመራ እየተደረገ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር ሶማሊያን ጨምሮ ቀውስ ውስጥ ናቸው ካላቸው አገራት ለመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎች በጊዜያዊነት ለስደተኞች ከለላ የሚሰጠውን አሠራር አቋርጧል።

"አገራችን ውስጥ አንፈልጋቸውም። እዚያው አገራቸው ሄደው የተሰበረውን ይጠግኑ" ብለዋል ትራምፕ።

ሶማሊያ የሕንድ ውቅያኖስ ያዋስናታል። በኤደን ባሕረ ሰላጤ ስትራቴጂክ አገርም ናት። የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርቷ ከዓለም ዝቅተኛው እንደሆነ የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።

54 በመቶ የአገሪቱ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።

ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ሶማሊያ ውስጥ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶችን ትፈጽማለች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሶማሊያ ዋነኛ መተዳደሪያዋ ግብርና ነው። ለዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት የተናጠች ሲሆን፤ የተለያዩ አገራት ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ጣልቃ ሲገቡም ቆይተዋል።

የመሐመድ ሲያድ ባሬ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1991 ከሥልጣን ከወረደ በኋላ ላለፉት አሥርታት ሶማሊያ በጦርነት እና በግጭት እየታመሰች ቀጥላለች።

በሞቃዲሹ ያለው የፌደራል መንግሥት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ሲሆን፤ እንደ አል ሻበብ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን በመዋጋት ረገድ የአፍሪካ ኅብረት በሚደግፈው ወታደራዊ ተልዕኮም የታገዘ ነው።

የጎሳ ግጭት፣ የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ማዕከላዊው መንግሥት ተቀባይነት ማጣቱ ሶማሊያ እንድትከፋል እና መረጋጋት እንዲርቃት ምክንያት ሆነዋል።

ቀድሞ በብሪታኒያ የሞግዚት አስተዳደር ሥር የነበረችው ሰሜናዊ ግዛት በ1991 ሶማሊላንድ በሚል ራሷን የቻለ አገር መሆኗን ብታውጅም ዓለም አቀፍ ዕውቅና አላገኘችም። ሆኖም ግን ከሞቃዲሹ መንግሥት ተነጥሎ አስተዳደሩን ቀጥሏል።

ከሶማሊላንድ በስተምሥራቅ የፑንትላንድ ግዛት በይፋ የፌደራል መንግሥቱ አካል ቢሆንም ራስ ገዝ አስተዳደር መሆኑን አውጇል። ባለፉት ዓመታት የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ታጣቂዎች ዋነኛ መንቀሳቀሻም ሆኗል።

በዴንማርክ ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ጄትሮ ኖርማን "በተራራማ አካባቢ ወደ 400 የሚደርሱ ታጣቂዎች እንደሸመቁ ይገመታል። ለኤደን ባሕረ ሰላጤ ያለው ቅርበት አካባቢውን ስትራቴጂያዊ አድርጎታል። ለዓመታት በጦርነት እየታመሰች ካለችው ከየመን የጦር መሣሪያ ማስገባትም ይቻላል" በማለት ያስረዳሉ።

አብዛኛውን ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል የሚቆጣጠረው ከአል-ቃይዳ ጋር ትስስር ያለው አል ሻባብ መዲናዋ ሞቃዲሹን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጽመው ጥቃት በርካቶች ተገድለዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ከአሜሪካ ዋነኛ ስጋቶች መካከል አንዱ ነው።

"ከግዛት ይዞታ አንጻር ከአል-ቃይዳ ክንፎች በአጠቃላይ ስኬታማው ነው ልንል እንችላለን" በማለት ተንታኙ ይገልጻሉ።

የሶማሊያ መንግሥት አል ሻባብን ከአጥቂነት ራሱን ወደሚከላከል ታጣቂ ቡድነት እንዳሸጋገረው ይናገራሉ።

"አሁን ግን መንግሥት ያገኘው ድል ባለበት እየተገታ ነው" ይላሉ። ይህንን ተከትሎም አል ሻባብ የሚቆጣጠራቸውን አካባቢዎች አስፋፍቷል።

የአል ሻባብ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በሶማሊያ ለምታደርገው ወደታራዊ ጥቃት ዋነኛ ኢላማ አል ሻባብ ነው

የአፍሪካ ኅብረት ወታደራዊ ተልዕኮ በመጠን እየቀነሰ መጥቷል። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት የአውሮፓ አገራት ድጋፍ መቀዛቀዝ ነው።

አል ሻባብን በመዋጋት ረገድ እምብዛም ለውጥ እየታየ አይደለም። የሚደረገው ድጋፍ ከመቀነሱ አንጻር በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የሶማሊያ ወታደሮች ታጣቂ ቡድኑን መቋቋም ተስኗቸዋል።

በሶማሊያ ጣልቃ ከሚገቡ የውጭ አገራት መካከል አሜሪካ፣ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይጠቀሳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2006 በአሜሪካ ድጋፍ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያን ወርረው ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ንቅናቄ የወለደውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን ከሥልጣን አስወግደዋል።

አስተዳደሩ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ ሶማሊያን ይቆጣጠር ነበር።

አስተዳደሩ በሶማሊያ ለመስፋፋት ያደረገው ጥረት በኢትዮጵያ ወታደሮች አማካኝነት ተገትቷል።

'የከሸፈ አገር' ምሳሌ ተደርጋ የምትጠቀሰው ሶማሊያ በዘርፈ ብዙ ቀውሶች እንደምትናጥ ተንታኙ ያሰምሩበታል።

በአገሪቱ በተንሰራፋው ግጭት እና ነውጥ ምክንያት የነዋሪዎች ሕይወት ሲመሳቀል፣ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም መፈጸማቸው ተዘግቧል።

በአውሮፓውያኑ 1992 ከሲያድ ባሬ አስተዳደር መንኮታኮት በኋላ የተለያዩ የጦር አበጋዞች ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ተስፋን መመለስ' (Restore Hope) የተባለ ዘመቻ ከፍተዋል።

የዘመቻው ዓላማ አገሪቱን ከረሃብ ማውጣት እና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋም ነበር።

የአሜሪካ ጦር ለዓመታት በሶማሊያ ተሰማርቶ ቆይቷል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 3/1993 በሞቃዲሹ አማጺ መሪዎችን ለመያዝ ልዩ ዘመቻ ተካሂዶ ነበር። ይህ ዘመቻ እንደታቀደው ስላልተከናወነ ሁለት የአሜሪካ 'ብላክ ሀውክ' ሄሊኮፕተሮች ተመትተው ወድቀዋል።

በሄሊኮፕተሮቹ ውስጥ የነበሩ ወታደሮችን ነፍስ ለማዳን ለሰዓታት በቀጠለ ውጊያ 18 የአሜሪካ ወታደሮች ተገድለዋል።

የወታደሮቹ አስከሬን በአደባባይ መጎተቱ አሜሪካውያንን ያስደነገጠ ክስተት ነበር።

የአሜሪካ ወታደሮች በሶማሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዴንማርክ ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ጄትሮ ኖርማን "በአሜሪካም በሶማሊያም ያ ክስተት አልተረሳም። አሜሪካ ለዓመታት በፈጸመችው የአየር ድብደባ ንጹሃን ስለተገደሉ እምነት ተሸርሽሯል" ይላሉ።

ከክስተቱ በኋላ አሜሪካ ያሰማራቸውን የእግረኛ ጦር ቁጥር ብትቀንስም በሶማሊያ ያላትን ተሳትፎ አልገታችም።

አብዛኞቹ ጥቃቶች በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የተፈጸሙ ናቸው። አሜሪካ ጥቃቶቹን የምትፈጽመው በዋነኛነት ጂቡቲ ውስጥ ካላት ወታደራዊ ሰፈር ነው።

በእነዚህ ጥቃቶችም አሜሪካ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚገዳደሩ "አሸባሪዎችን" ዒላማ እንደምታደርግ ትገልጻለች።

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት አሜሪካ በእግረኛ ጦር አልፎ አልፎ ከምትፈጽመው ጥቃት ባሻገር ወታደሮችን በቀጣናው ታሠለጥናለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሥልጣን ሲይዙ የአሜሪካን 'ማለቂያ አልባ ጦርነቶች' ለመግታት ቃል ገብተዋል።

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የአፍሪካ ዕዝ መሪ ጄነራል ማይክል ላንግሊ እንደተናገሩት ዘንድሮ አሜሪካ በሶማሊያ 25 የአየር ጥቃት ፈጽማለች። ይህም በ2024 ከተፈጸመው በእጥፍ ይበልጣል።

"አሜሪካ ጂሃዲስቶችን ለማስወገድ እየሠራች ነው" ብለዋል የጦር መሪው።

የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ግን በጥቃቱ የሚገደሉት ጂሃዲስቶች ብቻ ሳይሆኑ ንጹሃን ዜጎችም ጭምር ናቸው።

ሶማሊያ ውስጥ በሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ንጹሃን መገደላቸውን የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ አምኗል።

'ኤርዋርስ' የተባለው በጦርነት የተፈጸሙ ግድያዎችን የሚመዘግበው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም እንዳለው፤ አሜሪካ በሶማሊያ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከ92 እስከ 167 ንጹሃን ሰዎች እንደተገደሉ ይገመታል። ከእነዚህ መካከል ቢያንስ 25 የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው።

የአሜሪካ ጦር አውሮፕላን ሊነሳ ሲንደረደር

የፎቶው ባለመብት, US Africa Command

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው መስከረም ወር የአሜሪካ አውሮፕላኖች ሶማሊያ ውስጥ ጥቃት ፈጽመዋል

ተንታኙ እንደሚሉት የንጹሃንን ግድያ አል ሸባብ "ለፕሮፓጋንዳ ያውለዋል።"

"እነዚህ ጥቃቶች ለአል ሸባብ ያለውን ድጋፍ እንዲጠናከር ያደርጋሉ" ሲሉም ያስረዳሉ።

ተንታኞች የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታገን) የድሮን ጥቃት መፈጸምን እንደ ስትራቴጂ መያዙ ምን ያህል አዋጭ ነው? የሚለውን ጥያቄ ይሰነዝራሉ።

አሜሪካ ግቧ የፌደራል መንግሥቱን መደገፍ እና አገሪቱን ከቀውስ ማውጣት መሆኑን ብትገልጽም፤ ስኬታማነቷ ላይ ግን ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም።

"በዋነኛነት ጥረት እየተደረገ ያለው የሶማሊያ ችግር ድንበር እንዳይሻገር እና አል ሻባብ እንደ ኬንያ እና ኡጋንዳ ባሉ አጎራባች አገራት የሚያደርሰውን ጥቃት ለመገደብ ነው" ይላሉ ተንታኙ።

ትራምፕ አሜሪካ በሌሎች አገራት ያላትን ጣልቃ ገብነት እየተቹ ለምን በሶማሊያ የሚፈጸም ጥቃትን ይደግፋሉ? ለሚለው ጥያቄ እንደሚከተለው ምላሽ ሰጥተዋል።

"ይህ አስተዳደር በሶማሊያ የሚፈጸሙ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችን ከማስቆም ይልቅ እምብዛም የማይታዩ ማድረግ ይሻል። ወታደሮቹን ለአደጋ ሳያጋልጥ የድሮን ጥቃት መፈጸም ኃያልነቱን ለማሳየት ሊረዳው ይችላል።"

አሜሪካ በሶማሊያ የምትከተለው ፖሊሲ የታለመለትን ግብ እንደማይመታ ግምታቸውን የሚያስቀምጡ የፖለቲካ ተንታኞች ይደመጣሉ። አል ሻባብን በድሮን ጥቃት ብቻ ማስቆም አይቻል ይሆናል።

በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ የሰብአዊ መብት መርማሪ ኢሻ ዳይፋት እንደሚሉት በ2023 ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ለምግብ እጥረት ሲጋለጡ 730 ሕጻናት ሕይወታቸው ተቀጥፏል።

የአየር ንብረት ለውጥ የረሃብ መስፋፋትን እንዳባባሰው ያወጡት ሪፖርት ይጠቁማል።

ትራምፕ የአየር ንብረት ለውጥ በጋረጠው አደጋ አያምኑም። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅትን (ዩኤስኤአይዲ) እንዲሁም አሜሪካ በተባበሩን መንግሥታት አማካኝነት የምታደርገውን ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንድትቀንስም ውሳኔዎች አሳልፈዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በበኩሉ ሰብአዊ ቀውስን ለመግታት ለሚያደርገው ጥረት እያገኘ ያለው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ አስታውቋል።

ትራምፕ በሶማሊያ የሚከተሉት ወታደራዊ ስትራቴጂ ውጤታማ መሆኑ የሚታየው በጊዜ ሒደት ነው። ተንታኞች እንደሚሉት ግን የቅርብ ጊዜ የሶማሊያ ታሪክ ሲታይ እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት ጣልቃ ገብነት በጉልህ ይጠቀሳል።