ሐማስ በጋዛ ከሚደረገው ጦርነት ተርፎ ኅልውናው ሊቀጥል ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE / REX / Shutterstock
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ይህንንም ተግባራዊ ከማድረግ የማዘግየት ፍላጎት እንደሌላቸው "ማቆየት አልፈልግም" ሲሉ ነው የገለፁት።
ስለዚህ እስራኤል ጋዛን የምትቆጣጠር ከሆነ ለዓመታት ግዛቱን ሲያስተዳር የቆየው ሐማስ በግዛቲቱ ውስጥ የሚኖረው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ኔታንያሁ ፍላጎታቸውን ይፋ ያደረጉበትን መግለጫ ከመስጠታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ታጣቂው ቡድን ሐማስ፣ የፍልስጤም ሉዓላዊ መንግሥት እስካልተመሠረተ ድረስ ትጥቅ እንደማይፈታ በድጋሚ አረጋግጧል።
በዚህም በጋዛ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የእስራኤል ዘመቻ በማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በሚደረጉት ንግግሮች ላይ ለአንደኛው የእስራኤል እና የአሜሪካ ቁልፍ ጥያቄ ሐማስ የሰጠው ምላሽ ነው።
እስራኤል የሐማስን ትጥቅ መፍታት ግጭቱን ለማስቆም ለሚደረገው ማንኛውም ስምምነት ከበርካታ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል እንደ አንዱ ነው የምትመለከተው።
ባለፈው ሳምንት ሳዑዲ አረቢያ እና ፈረንሳይ በጋራ በመሩት እና ኒው ዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ 17 አገራት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአረብ ሊግ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
በዚህም ጦርነቱን ለማስቆም ሐማስ ትጥቅ እንዲፈታ እና በጋዛ ላይ ያለው ቁጥጥርን እንዲተው ጠይቀዋል።
በጋዛ እየተካሄደ ባለው ድርድር ውስጥ በአብዛኛው ሸምጋይ የሆኑት ግብፅ እና ኳታርም ስማቸው በመግለጫው ውስጥ የተካተተ ሲሆን፣ እስራኤል እና አሜሪካ ግን አልፈረሙም።
ሐማስ የትጥቅ ፍልሚያውን ይቀጥላል
አንድ የሐማስ መሪ ለአልጀዚራ ቡድኑ እንኳን ትጥቁን ሊፈታ "የተተኮሱ የጥይት ቀለሆችን" እንኳ አይሰጥም ብለዋል።
ይህ ንግግርም ቡድኑ የፍልስጤም መንግሥት እስካልተቋቋመ ድረስ የትጥቅ ትግሉን ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኑን ግልጽ የሚያደርግ ነው።
በጋዛ አል-ኡማ ዩኒቨርሲቲ የፍልስጤም ፖለቲካ መምህር የሆኑት ሆሳም አል ዳጃኒ ከጉባኤው በኋላ በወጣው የኒውዮርክ መግለጫ አንቀጽ 11 ላይ ከፍተኛ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንደተሰጠው ያምናሉ።
ከጉባኤው የወጣው ይፋዊው መግለጫ አንቀጽ 11 "በሁሉም የፍልስጤም ግዛቶች አስተዳደር፣ሕግ ማስከበር እና የፀጥታ ኃላፊነት በፍልስጤም አስተዳደር የሚመራ ይሆናል" ይላል።
አል ዳጃኒ በሰነዱ ውስጥ ከተካተቱት 41 አንቀጾች መካከል የተወሰኑት የፍልስጤም መንግሥት መመሥረት እና ከእስራኤል ጋር መኖርን የሚያመለክቱ ናቸው።
ይህ ማለት መግለጫው የፍልስጤም አገር መመሥረትን የሚያስችሉ በርካታ ዘዴዎችን ይጠቅሳል ብለዋል።
"የቀረው የኒውዮርክ መግለጫ ተግባራዊ ከሆነ አንቀጽ 11 ከወዲሁ ተቀባይነት አግኝቷል" በማለት አል ዳጃኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Amr Alfiky / Reuters
የፍልስጤም አገርነት
ሐማስ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች ምዕራባውያን አገራት በአሸባሪ ድርጅትነት የተፈረጀ ነው።
ፍልስጤም በአገርነት ተመሥርታ መንግሥት ሲኖራት ቡድኑ እጁ ያሉትን የጦር መሳሪያዎች ለወደፊቱ የፍልስጤም መንግሥት እንደሚያስረክብ አሳውቋል።
ነገር ግን ተንታኞች እንደሚሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት ሐማስ በጋዛ ላይ የነበረውን ቁጥጥር በእጅጉ አጥቷል።
ቢሆንም ግን ሐማስ አሁንም ድረስ እንደ ግዛቲቱ አስተዳዳሪ አካል ያለውን ቦታ እንደያዘ ነው።
ቡድኑ አዲስ ያቋቋመው ሳህም ወይም 'ዘ አሮው ዩኒት' የተባለው የደኅንነት ክፍል በሕዝቡ ውስጥ ሥርዓት ማስጠበቅ እና ዘረፋን መከላከልን ዓላማ አድርጎ እየሠራ ነው።
ፍልስጤማውያን ሲቪሎች በሐማስ ላይ ቁጣቸውን ሲገልጹ፣ተዋጊዎቹ በተቃውሞ ሰልፎች ላይ እርምጃ ወስደዋል።
በጋዛ የምግብ እርዳታ እጥረት ስላለ የእርዳታ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥታት ሰዎች በረሃብ እየሞቱ መሆናቸውን በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።
ብዙ ተንታኞች እንደሚሉት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲከፍት ተዋጊዎቹ ከጠበቁት በላይ የሆነ ሁኔታ እንደገጠማቸው እና ወደ እንደዚህ ዓይነት ደካማ አቋም ላይ እንገባለን ብለው አልጠበቁም ነበር።
እስራኤል በጋዛ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ባካሄደችባቸው ባለፉት 22 ወራት የሐማስ ተዋጊዎች ተዳክመዋል።
ጋዛ ውስጥ ያሉ ምንጮች እንደሚሉት ቡድኑ አሁንም የጦር መሳሪያ ቢኖረውም ክምችቱ ግን እያሽቆለቆለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ይህንንም ለመሸፈን ከእስራኤል ጥቃት የተራረፉትን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል እና በአብዛኛው ሳይፈነዱ የቀሩ ቦምቦችን በመጠቀም ላይ ነው።
የሐማስ ተዋጊዎች የእስራኤል ወታደሮችን ለማጥቃት የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማንሳት መልሰው ይጠቀማሉ፤ እንዲሁም በራሳቸው ፈንጂዎችን ይሠራሉ።
እስራኤል የቢቢሲ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ እንዳይገቡ በመከልከሏ የተባሉትን ጉዳዮች በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻልንም።
በአሁኑ ወቅት ሐማስ በቀጣናው የቀሩት አጋሮች ጥቂት ናቸው። በእስራኤል እና በኢራን መካከል ከተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት በኋላ ቴህራን ለሐማስ ድጋፍ የማድረግ አቅሟ ቀንሷል።
ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ እስራኤል መሪዎቹ ላይ በወሰደችው ጥቃት እና ግድያ ተዳክሟል።
ከሊባኖስን መንግሥት ትጥቅ እንዲፈታ ጥያቄ የቀረበለት ሔዝቦላህ ለሐማስ የውጭ ድጋፍ ለመስጠት ያለው ዕድል አነስተኛ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Dawoud Abu Alkas / Reuters
የአረብ ሊግ
የአረብ ሊግ ሐማስ ትጥቅ እንዲፈታ የሚጠይቀውን የኒው ዮርክ የአቋም መግለጫን ፈርሟል።
የአረብ ሊግ ወትሮም ለሐማስ ቦታ ሚሰጡ ወዳጅ የሆኑትን እንደ ኳታር ያሉ አገራትን ጨምሮ 22 አባላት አሉት።
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች የውይይት መድረክ ቻታም ሐውስ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዮሲ መከልበርግ "እስራኤል እና አሜሪካ የተለመደውን አቋማቸውን እንደያዙ ናቸው" ብለው ያምናሉ።
ነገር ግን "የአረብ አገራት አቋም ተቀይሯል" ይላሉ። ከአረብ አገራት እና ከቀጣናው ባለድርሻዎች የሚደርሰው ጫና ሐማስን "በጣም የተገለለ" ሊያደርገው እንደሚችል ጠቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ታጋቾች
በመስከረም 26/2015 ዓ.ም. ጥቃት ሐማስ የያዛቸው በእጁ ላይ የሚገኙ ቀሪ እስራኤላውያን ታጋቾች አሁንም ለቡድኑ ወሳኝ የመደራደሪያ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል።
ሐማስ በፈጸመው ታይቶ በማይታወቅ ጥቃት በወቅቱ ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 251 ሰዎች ታግተዋል።
በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው እስካሁን በቀጠለው ጦርነት ከ60 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
ከእስራኤላውያን ታጋቾች መካከል የተወሰኑት የሞቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ተለቅቀው ወደ እስራኤል መመለሳቸውን እና ቢያንስ 20 ቀሪ ታጋቾች በሕይወት እንዳሉ አሜሪካ ታምናለች።
በዚህ ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ሐማስ ከታጋቾቹ መካከል ኤቫታር ዴቪድ ተዳክሞ እና ተጎሳቁሎ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል።
ሐማስ ይህንን ቪዲዮ ያሠራጨው የታጋቾቹ ቤተሰቦች ጦርነቱን እንዲያቆሙ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ተጨማሪ ጫና ያሳድራሉ ብሎ ተስፋ በማድረግ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ቪዲዮው ከታየ በኋላ ቤተሰቦች ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።

ባለፉት 22 ወራት የተገደሉ የሐማስ መሪዎች
ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመበት መስከረም 2016 ዓ.ም. ወዲህ ኢራን ውስጥ ከተገደሉት የሐማስ ጠቅላይ መሪ እስማኤል ሃኒዬን ጨምሮ በርካታ የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮች ገድላለች።
የተፈጸመባትን ጥቃት እንደመራ በብዙዎች ዘንድ የሚታመነው ያህያ ሲንዋርን እዚያው ጋዛ ውስጥ ገድላዋለች።
እንደ መከልበርግ አመለካከት በጋዛ ውስጥ ያሉት የሐማስ መሪዎች በውጭ ካሉት የተለየ ፍላጎት አላቸው።
በቀዳሚነት በሕይወት ከመትረፍ ባሻገር "በጋዛ ውስጥ ያላቸውን ፖለቲካዊ ሚና እና አስፈላጊነትን ለማስጠበቅ ይሞክራሉ፤ ይህም አሁንም ስምምነት ላይ ለመድረስ የተወሰነ ድጋፍ አለው" ይላል።
ለዚህ ደግሞ ቡድኑ ሚናውን ይዞ ለመቆየት የቀሩት መሪዎቹ ከባድ ውሳኔዎችን ማሳለፍ አለባቸው።
ነገር ግን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋዛን "ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር" እና "ሐማስን ለማስወገድ" ያላቸውን ፍላጎት ካሳወቁ በኋላ ሐማስ ያለው ምርጫ ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሐማስ ዕጣ ፈንታ
ታዲያ ሐማስ በጋዛ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ሊተርፍ ይችላል?
የፍልስጤማውያን አገር እና መንግሥት ከተመሠረተ ሐማስ በገባው ቃል መሠረት የትጥቅ እንቅስቃሴውን ይተዋል።
ቢሆንም ግን አሁን ያለው የእስራኤል መንግሥት አቋሙን ካልቀየረ የፍልስጤም መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ በጣም ሩቅ ይመስላል።
ይህ ቢሆን እንኳን የሐማስ ኅልውና ያከትማል ማለት አይደለም።
የቻተም ሐውሱ ዮሲ መከልበርግ ሐማስ "ወደፊት መልሶ በማዋቀር" የፍልስጤም የፖለቲካ መድረክ አካል ሆኖ የመቀጠል ዕድል ሊኖረው እንደሚችል ተንብየዋል።
ይህም ከፍልስጤም ግዛት ውስጥ ወይም ከውጪ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው እስራኤል ሊቋቋም በሚችለው የፍልስጤም መንግሥት ላይ በሚኖራት አቋም እና አሁን እየተካሄደ ካለው አስከፊ ጦርነት በኋላ ሐማስ በጋዛ ነዋሪዎች ዘንድ በሚኖረው ተወዳጅ ላይ የሚመሠረት ይሆናል።















